የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ተገለጸ

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

የካቲት 23/2014 (ዋልታ) በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላትና ከመምህራን ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡

ለትምህርት ሥርዓቱ መውደቅ ጥራትን ያላማከለ የትምህርት ማስፋፊያና ተደራሽነት፣ የትምህርትና የፖለቲካ ሥርዓት መጣመር፣ የፖለቲካና ከባባዊነት መደባለቅ እንዲሁም በአገር ደረጃ ላይ የደረሰ የሞራል ክስረት በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕውቀት ማበልፀጊያ ሆነው ሳለ ከተልዕኳቸው ውጪ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማራመጃ መሆናቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ትውልዱ የሞራል ክስረት እንዳያጋጥመው ቤተሰብ፣ የትምህርትና የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም ተጠሪ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ርብርብ ማድረግ አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸውን ከዩኒቨርስቲው ኮሙዩኒኬሽን ለዋልታ የተላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

በአገር ዐቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት ትምህርት ሚኒስቴር ለአጠቃላይ ትምህርት ትኩረት መሰጠት እንዳለበት አምኖ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡

የተሻለች ኢትዮጵያን የሚመራና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የመጠቀ ዕውቀት ያለውን ትውልድ ለማፍራት ከአሁኑ የሥርዓተ ትምህርት ክለሳና ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ የትምህርቱ ሴክተር አመራር በመስጠት ድጋፋዊ ክትትል ማድረግ እንዳለበት በመድረኩ ተነስቷል፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ ከወደቀበት ችግር ለማላቀቅ ድክመቶቻችንም ነቅሰን በማውጣትና አመክኖአዊ አስተሳሰብና በማራመድ የላቀ አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ ማፍራት እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡