ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ ተያዘ

የካቲት 24/2014 (ዋልታ) በሐሰተኛ ሰነድ ወደ መሃል ሀገር ሊገባ የነበረ ግምታዊ ዋጋው ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ማዋሉን በጉምሩክ ኮሚሽን የአዋሽ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጽሕፈት ቤቱ የኮንትሮባንድ መከላከል ቡድን መሪ ኢንስፔክተር ዓለሙ ይመር ለኢዜአ እንደተናገሩት የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-62657-ኢትና የተሳቢ ቁጥር 18099 የሆነው ከባድ የጭነት ተሸከርካሪ በሁለት ኮንቴነሮች የጫነውን የኮንትሮባንድ ዕቃ ጨለማን ተገን በማድረግ ለማሳለፍ ሲሞክር ተደርሶበታል።
ዕቃው መነሻውን ድሬዳዋ በማድረግ በሚሌ-ኮምቦልቻ መሥመር ህጋዊ በማስመሰል ከውጭ ወደ መሃል ሀገር ለማስገባት የተዘጋጀ እንደነበረም አስረድተዋል።
ለዚህም የሚረዳው የተለያዩ ሐሰተኛ የጉምሩክ ሰነድና የኮንቴነር ማሸጊያ በመጠቀም እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የጉምሩክ ጣቢያዎችን ለማሳለፍ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።
ለጽሕፈት ቤቱ የመረጃ ሠራተኞች በደረሰ ጥቆማ መሠረት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በየካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ልዩ ቦታው “ብርጌድ” በተባለው ሥፍራ የኮንትሮባንድ ዕቃውን በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደቻሉ አስታውቀዋል።
ከ50 ሺሕ ስቴካ በላይ ሲጋራና ከ3 ሺሕ 700 ስቴካ በላይ ሺሻ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ውስጥ እንደሚገኙበት ኢንስፔክተር ዓለሙ ጠቅሰዋል።
የተሽከርካሪው ሾፌርና ረዳቱ በህግ ቁጥጥር ሥር ውለው ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ዕቃዎቹን ለማሳለፍ ተባባሪ በመሆን ከተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች መካከል አንድ የ”አርበረከቴ ” ፍተሻ ጣቢያ ሠራተኛ በቁጥጥር ሥር መዋሉንና ሌላውን ለመያዝ ክትትል እየተደረገበት እንደሚገኝ ቡድን መሪው አብራርተዋል።