አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን በማሳደግ የምጣኔ ሃብት እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል ተባለ

የካቲት 25/2014 (ዋልታ) አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን በማሳደግ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማትን በማሳደግ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ብዝሃነት በማስፋትና ሁሉን አቀፍ እድገት በማምጣት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ ምክክር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ምክክሩ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የተባበሩት መንግሥታት ንግድና ልማት ኮንፈረንስ በጋራ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶችን በማዘጋጀት በኩል ከ1957 ዓ.ም የጀመረ የዳበረ ልምድ እንዳላት ገልጸዋል።
በዚህም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ፣ ድህነትን መቀነስና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት እንደተቻለ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2019 የጀመረችው አካታች ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለያዩ ዘርፎች ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑንም በተግባር አረጋግጠናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአመራሩ ቁርጠኝነት በመታገዝ በኮቪድ-19 ወረርሽኝም እየተፈተነች ቢሆንም የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅሰዋል።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንዱስትሪውን በማጎልበት ሁሉን ዐቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና በቻይና መንግሥት በኩል የተመቻቸውን ግሪንሌይ የገበያ እድል በአግባቡ ትጠቀምበታለችም ነው ያሉት።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገራዊውን ጥቅል ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአገሪቱ የተፈጠረውን የሥራ እድል አምስት በመቶ የያዘ መሆኑን ገልጸው እ.ኤ.አ እስከ 2030 ወደ 15 በመቶ የማሳደግ ትልም እንዳለም ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት በማደግ ላይ ያሉ አገራት ልዩ መርሃ ግብር የአፍሪካ ዳይሬክተር ፖል አኪውሚ ታዳጊ አገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የምርት ትስስር፣ የሥራ እድል ፈጠራ አቅምና ምርታማ ሃብቶችን መለየት አለባቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ5 ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ማመንጨት የሚችለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች አቅሟን እየተጠቀመች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዳላት ጠቅሰው የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደምትችልም ማሳያ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡