ተቋሙ እውነትን ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል – ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ

የካቲት 25/2014 (ዋልታ) ኢዜአ እውነትን ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር ለኢትዮጵያ የቀጣይ ጉዞ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢዜአ 80ኛው ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ሲሆን በዛሬው እለትም ዓውደ ርእይ የተከፈተ ሲሆን የፓናል ውይይትም ይካሄዳል ተብሏል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር ኢዜአ በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችን በማፍራት ለኢትዮጵያ የሚዲያ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ዜና የታሪክ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው ኢዜአ ያለውን የበርካታ ዓመታት ልምድ ተጠቅሞ ታሪክ የመሰነድ ሥራውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዘላቂ፣ ቋሚና አገር አሻጋሪ ተቋማትን መፍጠርና ማጠናከር አሁን ላለው መንግሥት ወሳኝ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ አስነብቧል፡፡

በተቋሙ ያለፉ ባለሙያዎች ለአገር በጎ ነገሮችን አበርክተዋል በሥነ ጽሑፍ ረገድም ጉልህ ድርሻ ማበርከታቸውን ገልጸው ተቋሙ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ የሙያ ተቋማት እንዲጠናከሩ መሥራት እንዳለበት አሳስበዋል።