ኢትዮጵያና ጂቡቲ በባሕር – አየር ሎጅስቲክስ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ተፈራረሙ

የካቲት 25/2014 (ዋልታ) የኢትዮጵያና የጂቡቲ አየር መንገዶች፣ የጅቡቲ ዓለም ዐቀፍ ነጻ ቀጣና እና ወደብ ባለስልጣን እንዲሁም የዶራሌ ደረቅ ጭነት ወደብ አገልግሎት በባህር – አየር ሎጅስቲክስ ላይ በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ኃላፊ አምባሳደር መሐመድ ሀሰን እና የጅቡቲ ነፃ ቀጣና እና ወደብ ባለሥልጣን ሊቀመንበር አቡበከር ኦማር ሃዲ ተገኝተዋል።

በዘርፉ የተፈረመው የሁለቱ አገራት የአጋርነት ሥምምነት ቀጣናዊ ትሥሥሩን ይበልጥ በአየር፣ በየብስ እና በባሕር በማሳለጥ ያጠናክራል ተብሎለታል፡፡

በባህር – አየር የሚሠጠው የጭነት አገልግሎት በባህር ብቻ ከሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት በሁለት እጥፍ የተቀላጠፈ እና በአየር ከሚሰጠው የጭነት አገልግሎት አንጻርም ክፍያው በሁለት እጥፍ እንደሚያንስ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአፍሪካን ንግድ፣ ግብይት እና ኢንቨስትመንትን በማነቃቃት እና በማሳለጥ ረገድ የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የአሁኑ ስምምነትም የወደብ አገልግሎት እና ትራንስፖርት ዘርፉ ላይ የላቀ እመርታ እና ትርፍ እንዲኖር ያግዛል ነው የተባለው፡፡

ከዚህ ባለፈም የእውቀት ሽግግር እንዲኖርና በቀጣይም አገራቱ ፖሊሲዎቻቸውን ከኢኮኖሚያቸው ጋር በማጣመር ለዕድገታቸው የሚሰሩበትን ምህዳር እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ የባሕር-አየር ካርጎ አገልግሎትን ለመጀመር የዛሬ ዓመት የተስማሙ ሲሆን በዛሬው እለትም በይፋ ስምምነቱን ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ የሸቀጦችን ዝውውር በማቀላጠፍ የአኅጉሪቱን ንግድ ይበልጥ ማሳለጥ እንደሚያስችል ሲታመን አገራቱም በአገልግሎቱ ላይ ባለፈው አነድ ዓመት ሲሰሩ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

የአገልግሎቱ መጀመር በተለይ ከቻይና ወደ አፍሪካ የሚሻገረውን ምርትና ሸቀጥ በባሕር-አየር የጭነት አገልግሎት በማያያዝ ከጂቡቲ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት ፈጣን የካርጎ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያስችል ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡