ጉባኤው በሰላም ግንባታ ዙሪያ ለሚያከናውነው ተግባር ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገለት

የካቲት 26/2014 (ዋልታ) ስተርሊንግ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በአገር ዐቀፍ ደረጃ በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ዙሪያ ለሚያከናውነው ተግባር የሚውል ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እ.አ.አ በ2022/23 በኢትዮጵያ በተለያዩ ክልሎች ሊሰራው ያሰበውን የሰላም ግንባታ፣ የግጭት አፈታትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክር የበጀት ድጋፍ እንደተደረገለት የጉባኤው ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ታጋይ ታደለ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ጉባኤው የበጀት ድጋፉን ያገኘው መቀመጫውን በአሜሪካ ዩታ ግዛት ካደረገው ስተርሊንግ ፋውንዴሽን ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት መሆኑን ነው የገለጹት።
ጉባኤው እቅዱን ለመፈጸም የሀብት ማፈላለጊያ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል በማዘጋጀተ ለፋውንዴሽኑ የላከ ሲሆን ፋውንዴሽኑም ፕሮጀክቱን በመቀበል፣ የበጀት ድጋፍ ለማድረግ ፈቅዷል ነው ያሉት።
በዚህም መሠረት ጉባኤውና ፋውንዴሽኑ የድጋፍ ስምምነት ፊርማ ዛሬ በአሜሪካ ዮታ ግዛት አከናውነናል ብለዋል።
ፋውንዴሽኑ ከዚህ በፊትም ለጉባኤወ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበረና በቅርቡም ለጉባኤው የተሽከርካሪ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።