በአንኮበር የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞችን ለመደገፍ የተራራ ላይ የእግር እና የብስክሌት ጉዞ ተካሄደ

የካቲት 27/2014 (ዋልታ) በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በፀጥታ ችግር ምክንያት ተፅዕኖ የደረሰባቸውን የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ሰራተኞችን ለመደገፍ የገቢ ማሰባሰቢያ የተራራ ላይ የእግር እና የብስክሌት ጉዞ በሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ በመሀል ወንዝ ቀበሌ ተካሄደ።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ራይድ ዘ ሪፍት (ride The Rift) በሚል ከ3 አስጎብኚ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን ከየካቲት 25 እስከ 27 የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያካሂድ ቆይቷል።

የጫካ ውስጥ የእግር ጉዞ፣ ሩጫ እና የፓራ ግላይዲንግ (የአየር ቀዘፋ) ለገቢ ማሰባሰቢያው የተካሄዱ ሌሎች ትዕይንቶች ናቸው።

በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ከዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የተወጣጡ 40 የሚሆኑ የብስክሌት ጋላቢዋች፤ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች እና የኤምባሲ ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

ለ3 ቀናት የተካሄደው ዝግጅት ዛሬ ሲጠናቀቅ የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እና ሌሎች የሚኒስቴሩ ሰራተኞች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

መሰረት ተስፋዬ (ከአንኮበር)