በ400 ሺሕ ሄክታር መሬት የበጋ ስንዴ ምርት ልማት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ

የበጋ ስንዴ ምርት ልማት

የካቲት 28/2014 (ዋልታ) በአገር ዐቀፍ ደረጃ ዘንድሮ በ400 ሺሕ ሄክታር መሬት የበጋ ስንዴ ምርት ልማት እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ እንደገለጹት በአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድ ስንዴን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እቅድ ተይዟል።

ይህን ተከትሎም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት ከባለኃብቶችና ከአርሶ አደሩ ጋር በመተባበር ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።

የስንዴ ምርት ቀደም ሲል በክረምት ወቅት የሚለማ መሆኑን አስታውሰው አሁን ላይ ዓመቱን ሙሉ ለማልማትና ምርቱን ለመጨመር የበጋ ወቅትን መጠቀም አስፈልጓል ብለዋል።

የበጋ ስንዴ ልማት ሥራዎች አምና ለስንዴ ምርት ጥቅም ላይ ይውል የነበረውን 180 ሺሕ ሄክታር አሁን ላይ 400 ሺሕ ሄክታር መድረሱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዚህ የእርሻ መሬት 16 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አመላክተዋል።

ሌላው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎችን አሟጦ በመጠቀም ረገድ ሦስት አማራጮች ተዘጋጅተው በዚሁ መሰረት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል በመስኖ አምራች ያልነበሩ አካባቢዎች ወደ ምርት እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW