የፓርቲው አንደኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች የቅድመ ጉባዔ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ

የካቲት 28/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች የቅድመ ጉባዔ ውይይት በአዳማ ከተማ ማካሄድ ጀመሩ፡፡
በጉባዔ ዝግጅት ሂደት በተካሄዱ ሀገር ዐቀፍ የፓርቲ ኮንፈረንሶች መላው የብልፅግና ፓርቲ አባላት በጉባዔው በቀጥታ በመሳተፍ የሚወክሏቸውን መምርጣቸው ይታወቃል፡፡
እነዚህ ውክልና የተሰጣቸው የጉባኤ አባላት በዛሬው ዕለት በአዳማ ከተማ ውይይት እያካሄዱ ሲሆን የቅድመ ጉባዔ ውይይቱ እስከ መጋቢት 1/2014 ዓ.ም የሚቆይና በጉባዔ ሪፖርት እና በቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ሪፖርት እንዲሁም በፓርቲው ህገ ደንብና ፕሮግራም ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ውይይቱን ያስጀመሩት የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አደም ፋራህ ባደረጉት ንግገር “የቅድመ ጉባዔ ውይይቱ በፓርቲው አመራር ሀገራችን ስኬቶችን ባስመዘገበችበት ወቅት እና በበሳል አመራር ሰጪነት ልንፈታቸው በሚገቡ ሀገራዊ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆነን የምናካሂደው ነው” ብለዋል፡፡
በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠንን ኃላፊነት እና እምነት ከዳር ለማድረስ በወንድማማችነትና አብሮነት መንፈስ መስራት ይገባናል ያሉት አቶ አደም “በቅድመ ጉባዔ የሚካሄደው ይህ ውይይት ለአንደኛ ጉባዔያችን ስኬታማነት ቁልፍ አስተዋፅኦ አለው” ነው ያሉት፡፡
በውይይቱም 1 ሺሕ 600 ጉባኤተኞች እየተሳተፉ መሆናቸውን ከብልጽግና ፓርቲ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡