በቡድን እና በተናጠል ተሽከርካሪዎችን ሲሰርቁ የነበሩ 21 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የካቲት 29/2014 (ዋልታ) በቡድን ተሽከርካሪዎችን ሲሰርቁ የነበሩ 21 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።
የልዩ ልዩ እና የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ከክትትል ክፍሉ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት በ3 ቡድን የተደራጁ 16 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ችለዋል።
በተመሳሳይ በተናጠል የመኪና ስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ 5 ግለሰቦችንም በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ የተደራጁ ወንጀሎች ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ያሬድ አለማየሁ በከተማዋ በተለያየ ጊዜ ተሽከርካሪዎች ተሰርቀው አካላቸው ተበታትኖ ለሽያጭ መቅረባቸው እንደተደረሰበት ገልፀዋል።
በዚህም በተደረገ ከፍተኛ ርብርብ የተሰረቁ ተሽከርካሪዎችን ማስመለስ መቻሉንም ዋና ኢንስፔክተሩ አስታውቀዋል።
በአጠቃላይ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በተደረገ ሰፊ ምርመራ እና ክትትል 9 ተሽከርካሪዎች መሰረቃቸውን በማረጋገጥና ከያሉበት በማስመለስ ተጠርጣሪዎች በ10 መዝገቦች ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሆነ መናገራቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የተሽከርካሪ ባለንብረቶች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።