ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የተሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያዊያንና ኤርትራዊያን የተሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፍ በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት ተካሄደ፡፡

ሰልፉ የተካሄደው ሕጉን ባረቀቁት የኒው ጀርሲ የኮንግረስ አባል ቲም ማሊኖውስኪ የሚሰሩበት ቢሮ ፊት ለፊት ሲሆን እሳቸውንና ሕጉን የሚቃወሙ መልዕክቶች በሰልፉ ላይ መተላለፉን ኢዜአ ከሰልፉ አስተባባሪዎች ያገኘው መረጃ አመላክቷል።

የዳያስፖራው ተወካዮች ሕጉን በአሜሪካ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት እንደሚቃወሙትና አፍራሽ ከሆነ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለኮንግረስ አባሉ ተወካዮች ሰጥተዋል።

ቶም ማሊኖውስኪ ያረቀቁት ሕግ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት የሚጎዳና የሁለቱን አገራት የማይጠቅም እንዲሁም በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድር መሆኑን ለተወካዮቻቸው የማስረዳት ሥራ መከናወኑ ተገልጿል።

“ቶም ማሊኖውስኪ ሽብርተኞችን መርዳት ያቁሙ ‘ኤችአር 6600’ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ነው” የሚል መልዕክት የያዘ ባነር አውሮፕላን በኮንግረስ አባሉ ቢሮ ሲያንዣብብ እንደነበረም ተገልጿል።

ረቂቅ ሕጉ ኤርትራንም የሚመለከት በመሆኑ በሰልፉ ላይ በአሜሪካ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በተጨማሪ ኤርትራዊያንም ተሳትፈውበታል።

በቀጣይ በአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ለማካሄድ መታሰቡ ተነግሯል።

ረቂቅ ሕጉን የሚቃወሙ እንዲሁም በአሜሪካ ኮንግረስ ለውይይት ቀርቦ ውሳኔ እንዳይሰጥበት ለማድረግ ዘመቻዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ ተመልክቷል።

የ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን በመቃወም በአሜሪካ ኒውጀርሲ ግዛት የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተስፋ ለኢትዮጵያ ከ’አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌርስ ኮሚቴ’ (ኤፓክ)፣ ኤርትራ አሜሪካዊያን ብሔራዊ ምክር ቤትና ሰላምና አንድነት የዋሺንግተን ዲሲ ግብርኃይል ጋር በመተባባር ያዘጋጀው እንደሆነም ተገልጿል።