የብልፅግና ፓርቲ 1ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ለመሳተፍ የተለያዩ አገራት እህት ፓርቲ አመራሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው

መጋቢት 2/2014 (ዋልታ) ከዛሬ መጋቢት 2 እስከ 4/2014 በሚካሄደው የብልፅግና ፓርቲ 1ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ የሚሳተፉ የተለያዩ አገራት እህት ፓርቲ አመራሮች ከትናንት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

በዚህም የዩጋንዳ ‘ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት’ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አልፔር ሲሞን ፒተር፣ የፓርቲው ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ አባል ሚስ አጋታ ናሉብዋም እንዲሁም የፓርቲው የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አዊች ፖላር ዛሬ አነጋግ ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።

እንግዶችን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ፍስሐ ሻውል አቀባበል እንዳደረጉላቸው ኢዜአ ዘግቧል።

በፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የሚመራው የዩጋንዳ ‘ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቨመንት’ (ኤንአርኤ) የነጻነት እንቅስቃሴ በሚል እ.አ.አ በ1986 የተመሰረተ ፓርቲ ነው።

በተመሳሳይም የቱርክ ገዥ ፓርቲ የሆነው የፍትህና ልማት ፓርቲ (AKP) የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ምክትል ሊቀመንበር ፌቭዚ ሻንቬርዲና የቱርክና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ቡድን ኃላፊ መህመት ሳይት ኪራዞግሉ በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ ለመታደም ትላንት ሌሊት አዲስ አበባ ገብተዋል።

እንግዶቹ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ደመቀ አጥናፉ አቀባበል አድርገዋል።

እ.አ.አ በ2001 ከተለያዩ የቱርክ ፓርቲዎች በተወጣጡ ፖለቲከኞች የተመሰረተው የቱርክ የፍትህና ልማት ፓርቲ(ኤኬ ፓርቲ)  ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ ቱርክን እየመራ የሚገኝ ፓርቲ ሲሆን የፓርቲው መሪ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን መሆናቸውም ተመላክቷል።