ቢሮው ባለፉት 7 ወራት ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ሰበሰበ

መጋቢት 02/2014 (ዋልታ) ባለፉት 7 ወራት ከ7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሰቡን የደቡብ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው የሰባት ወራት እቅድ አፈጻጸሙንና የሴክተር ጉባኤውን በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡
አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ ከተጀመረ ወዲህ በየዓመቱ የገቢ እድገት እየተመዘገበ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ዘይቱና ኢብራሒም ገልጸዋል።
የዘንድሮ ዓመት ገቢ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ እድገት ማሳየቱን የጠቆሙት ኃላፊዋ በህገ-ወጥ ደረሰኝ ገቢ የሚሰበስቡ እንዲሁም ግብርና ታክስ የሚሰውሩ ዜጎች በመኖራቸው በዘርፉ የተፈለገውን ያህል ውጤት እንዳይመዘገብ ትልቅ ተግዳሮት መሆኑን አስረድተዋል።
በመሆኑም እነዚህን ችግሮች መቅረፍ እና በቀጣይ የአፈጻጸም ጉድለቶችን ማረም እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከ705 በላይ በሚሆኑ ነጋዴዎች እና በልዩ ልዩ ህገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲሁም ደረሠኝ ማጭበርበር ላይ የተገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ላይ የገንዘብ ቅጣትን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎች መወሰዳቸውን የደሬቴድ መረጃ አመላክቷል።
የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡ 38 ባለሙያዎች የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ፣ የደመወዝ ቅጣት እንዲሁም ከሥራ እንዲሰናበቱ ሲደረግ በወንጀል የተከሰሱ 19 ሰራተኞች ደግሞ ጉዳያቸው በፍርድ ቤቶች እየታየ እንደሚገኝም ኃላፊዋ አብራርተዋል።
ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከ8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡