ለታራሚዎች የቲቢ በሽታ ምርመራ እና ልየታ ተደረገ

መጋቢት 5/2014 (ዋልታ) በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች የቲቢ በሽታ ምርመራ እና ልየታ ተደረገ።

መጋቢት 15 ቀን የሚከበረውን የዓለም የቲቢ ቀንን ምክንያት በማድረግ የቲቢ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የምርመራና ልየታ ሥራ ተከናውኗል፡፡

ሪች ኢትዮጵያ የተሰኘው አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅትም ከዩ ኤስ ኤድ ባገኘው ድጋፍ ለቲቢ በሽታ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የመለየት ሥራ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች የልየታና ምርመራ ዘመቻውን ያስጀመረ ሲሆን ዘመቻው ለቀጣይ 10 ቀናት ይቆያል ተብሏል።

“ሪች ኢትዮጵያ ቲቢን ለማጥፋት የድርሻችን እናበርክት፤ ህይወት እንታደግ” በሚል መሪ ቃል ከጤና ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባባር የቲቢ ቀንን ስለበሽታው ግንዛቤ በመፍጠር፣ የልየታና ምርመራ ሥራዎችን በማከናወን እንደሚያከብር አስታውቋል፡፡

የቲቢ ቀን በኢትዮጵያ ለ25ኛ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ40ኛ ጊዜ እንደሚከበርም ተገልጿል፡፡
በትዕግሥት ዘላለም