አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ 33 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ

መጋቢት 5/2014 (ዋልታ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል 20 ሚሊዮን ብር እና 13 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የዓይነት ድጋፎችን አደረገ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጣሰው ወልደሃና (ፕ/ር) በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በነበረው ጦርነት የተጎዱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም 10 ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በመሆን መልሶ ለማቋቋም በጋራ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለትም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥሩ ከሚገኙት ከሁሉም ኮሌጆች ያሰባሰበውን 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የዓይነት ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ድጋፉን የጫኑ ተሽከርካሪዎች በዛሬው እለት ወደ ሥፍራው እንደሚያቀኑና 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ድጋፎችም በቀጣዮቹ ቀናት ወደ ሥፍራው እንደሚያመሩ ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለወሎ ዪኒቨርሲቲ ድጋፉ የሚውል 20 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ድጋፉን ማድረጉ የወሎ ዩኒቨርሲቲ መልሶ እንዲቋቋምና የመማር ማስተማሩ ሥራ በአግባቡ እንዲያከናውን እንደሚረዳውም ጠቁመዋል።

ይህም ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ጠቃሜታ እንዳለው መናገራቸውን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በሰሜኑ የአገሪቱ ጦርነት የወደሙ ተቋማት መልሶ የመገንባት ሂደቱ ወደ ቀድሞ ሥራቸው እስኪመለሱ ሁሉም ተቋማት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናከረው እንዲቀሉም ጥሪ አቅርበዋል።