የአረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካ ችግሮቹ ተቀርፈው ወደ ምርት እንዲገባ ድጋፍ እንደሚደረግለት የማዕድን ሚኒስትሩ ገለጹ

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) የአረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካ በሦስት ወራት ውስጥ ያሉበት ችግሮች ተቀርፈው ወደ ምርት እንዲገባ እና ሴራሚክ ለገበያ ማቅረብ እንዲጀምር ለማስቻል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግለት የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

ሚኒስትሩ ከአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ጀምበር (ዶ/ር) ጋር የሴራሚክ ምርት ለማምረት ችግር እየገጠመው ያለውን የአረርቲ ሴራሚክ ፋብሪካ ጎብኝተዋል፡፡

ፋብሪካው በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአረርቲ የሚገኝ ሲሆን የማምረት አቅሙም በቀን 20 ሺሕ ሜትር ስኩዌር ሴራሚክ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የማዕድን ሚኒስትሩ በማኅበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ይህ ግዙፍ ፋብሪካ ምርቱን ለመቀጠል የኤሌክትሪክ ኃይልና የግብአት እጥረት እያጋጠመው መሆኑን በጉብኝታቸው ወቅት መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ለሌሎች ከፋብሪካው የተነሱ ችግሮችም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመስራት መፍትሄ እንሰጣለን ብለዋል።