ሚኒስቴሩ የከተማ ሕዝብ ከመንግሥት የሚጠብቀውን የመልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ ገለጸ

መጋቢት 7/2014 (ዋልታ) የከተማ ሕዝብ ከመንግሥት የሚጠብቀው የመልማት ፍላጎት እና ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ሌት ተቀን እንሰራለን ሲሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በከተሞች ተቋማዊና መሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የከተሜነት ምጣኔ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ መምጣቱን የገለጹ ሚኒስትሯ ከከተሞች ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ መልካም አጋጣሚዎች እንዳሉ ሁሉ በኅብረተሰቡ ፍላጎት መጨመርና ተያያዥ ጉዳዮች ምክንያት በርካታ የልማት፣ መልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች ይነሳሉ ብለዋል።

በተለይም በከተሞች ቀልጣፋ የሆነ የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ተግባራዊ እንዲሆን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በከተሞች የሚስተዋሉ መሰል ችግሮች በመንግሥት አቅም ብቻ ለመቅረፍ የሚቻል ባለመሆኑና የገንዘብ አቅም ውስንነት በመኖሩ መንግሥት ከአበዳሪና ለጋሽ ተቋማት ጋር በመተባበር ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ ውብና ለኑሮ ተስማሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርጾ ተግባራዊ እያደረገ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ የሚገኙ ከተሞች በቂ የመሰረተ ልማት የሌላቸው በመሆኑ መንግሥት ደረጃ በደረጃ የልማት ስርጭትን እንደሚያረጋገጥ ሙሉ እምነት እንዳላቸው መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።