የመከባበርና የመቻቻል እሴታችን እየተሸረሸረ በመምጣቱ በርካታ ችግሮች እየተከሰቱ ነው – የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) የመከባበርና የመቻቻል እሴታችን እየተሸረሸረ በመምጣቱ በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች እየተከሰቱ ነው ሲሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ፡፡

ኢትዮጵያ ለዘመናት የቆየ የመቻቻል፣ የመከባበርና አብሮ የመኖር ባህልና እሴት ያላቸው ሕዝብ መኖሪያ ነች፡፡
እነዚህን የማኅበራዊ መስተጋብር እሴቶች ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል ያደረጉ፤ ለገጠሙን ማኅበራዊ ቀውሶች መድኃኒት የሆኑ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ለዘመናት ይዛ የቆየችው የመከባበርና የመቻቻል እሴት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ምክኒያቶች እየተሸረሸረ በመምጣቱ የተነሳ በኢትዮጵያ በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች እየተከሰቱ እንደሚገኝ ቆይታቸውን ከዋልታ ጋር ያደረጉ የእናት ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

ማኅበራዊ ግንኙነታችን እንዲዳብርም ቤተሰብን ጨምሮ መገናኛ ብዙኃን ያሉንን መልካም እሴቶች አጉልቶ ማሳየት ይኖርባቸዋል ያሉት የእናት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ጌትነት ወርቁ እና የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ገ/ሚካኤል ረዳኢ መንግሥት የሚስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ የማውጣቱ ሂደት ላይ ትኩረት ሰጥቶ ከሰራ እሴቶቻችንን መመለስ እንችላለን ብለዋል፡፡

እየተዳከሙ የመጡ እነዚህን ማኅበራዊ መስተጋብሮቻችን እንዲዳብሩና እንዲጎለብቱ ከተፈለገ ደግሞ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሊሰራ ይገባል ነው ያሉት፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከንግግር ጀምሮ እስከ አለባበስ ያሉንን ባህሎች በማስተዋወቅ ረገድ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የጋራ እሴቶቻችንን በማጠናከር እና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ፖለቲከኞቹ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በሱራፌል መንግሥቴ