ሸኔ የሽብርተኛውን ሕወሓት ተልዕኮ ተቀብሎ ሕዝብ ላይ ጥቃት እየፈፀመ ነው – ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ሽብርተኛው ሸኔ የአሸባሪውን ሕወሓት ተልዕኮ ተቀብሎ ሕዝብ ላይ ጥቃት እየፈፀመ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ከጨፌ ኦሮሚያ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡
የጨፌ ኦሮሚያ አባላት በዋናነት በክልሉ እየተስዋለ ስለሚገኘው የሰላም መደፍረስ እና የህግ የበላይነት አለመከበር እንዳሳሰበቸው በስፋት አንስተዋል።
የመሰረተ ልማት ተደራሽነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እና የሥራ አጥ ቁጥር ማሻቀብ፣ ክልሉ ድንበር ከሚዋሰንባቸው አከባቢዎች የሚፈጠሩ ግጭቶችን በተመለከተ ጥያቄ አንስተዋል።
በዚህም ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ሸኔ የሕዝብም የራሱም አላማ እንደሌለው ገልጸው የሽብር ቡድኑ የሕወሓት ተልዕኮን ተቀብሎ ሕዝብ ላይ ጥቃት እየፈፀመ ነው ብለዋል።
የክልሉ መንግሥት ምንም አይነት ችግር በሰላም ለመቋጨት ፍላጎት እንዳለውና ነገር ግን ሀገር ካላፈረስን ከሚሉት ጋር ድርድር እንደሌለው አስታውወዋል።
ሳያውቁ ሽብርተኛ ቡድን በሕዝብ ስም በመደራጀቱ እውነት እየመሰላቸው ቡድኑን የሚቀላቀሉ ወጣቶች እንዳሉ እናውቃለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህ በሰላም ወደ ሕዝባቸው እንዲመለሱ ፍላጎት ስለመኖሩም አንስተዋል።
ይሁን እንጅ ከዚህ ውጭ የሆኑ የሕዝብ ጠላት ግን ማስተካከያ ሊወሰድበት ይገባል ብለዋል።
የክልሉ ነዋሪዎች በሽብርተኛው ሸኔ እየደረሰበት ያለውን የሰላም እጦት እና የድንበር ችግር በተመለከተ ምላሻቸውን ያከሉት የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ ፍቃዱ ተሰማ ለሽብርተኛው ሸኔ በክልሉ መሥፋፋት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ጦርነት እና በሚወሰደው ኦፕሬሽን አለመናበብ መኖር ዋና ምክንያት ነበር ብለዋል።
በተለይም የሽብር ቡድን ሕወሓት ወረራ መፈፀሙን ተከትሎ የክልሉ ልዩ ኃይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጋር መዝመቱ የኃይል አለመመጣጠን እንዲፈጠር ምክንያት እንደነበር አስታውሰዋል።
ነገር ግን በተለያዩ ግዜያቶች በርካታ ኦፕሬሽኖች ተካሂዶ በሽብር ቡድኑ ላይ እርምጃ ሊወሰድ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በክልሉ በሸኔ እና ደጋፊዎቹ የተከፈተው ጦርነት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሽብር ቡድኑ ሕወሓት ጋር ከሚደረገው ጦርነት ጋር የሚስተካከል ነው ያሉት የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ በተለይም የኢትዮጵያን መፍረስ የሚፈልጉ ህገወጥ አካላት የሚችሉትን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ነው ያነሱት።
ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የክልሉ መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አክለዋል።
ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ግን በወንድማዊነት እና አንድነት መንፈስ በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ችግሩን ከስሩ ለማጥፋት ግን የሁሉም ኃላፊነት እና አንድነት ያስፈልጋል ብለዋል።

በሚልኪያስ አዱኛ