በኦሮሚያ ክልል ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናገሩ

መጋቢት 12/2014 (ዋልታ) የኦሮሚያ ክልል ምጣኔ ሀብት ተወዳዳሪ ለማድረግ ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ፡፡
ጨፌ ኦሮሚያ እያካሄደ ባለው 1ኛ ዓመት 6ኛው የሥራ ዘመን 2 መደበኛ ጉባኤ ላይ ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት አንዱ ነው።
ይህን ዘርፍ ለመቀየር እና አቅም ያለው ምጣኔ ሀብት ለመገንባት አራት ዋና ዋና ጉዳዮች ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ጠንካራ አመራር ወይም አስተዳደር፣ ሰፊ እና ተደራሽ የምጣኔሃብታዊ እድገት መፍጠር፣ ቆጣቢ ማኅበረሰብ እና ዓለም ዐቀፍ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ መፍጠር ነው ብለዋል።
ይህን ለማሳካት ያስችል ዘንድ ክልሉ ልዩ ትኩረት በግብርናው ላይ አድርጓል ብለዋል።
ለዚህ ማሳያ ከሦስት ዓመት በፊት ከ7 ሺሕ ሄክታር ባልበለጠ መሬት ላይ የተጀመረው እና በሚቀጥለው ዓመት ከ1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ይሸፍናል ተብሎ የሚጠበቀው የበጋ መስኖ ስንዴ እርሻን በምሳሌነት አንስተዋል።

ለሌሎች የግብርና ዘርፎች የተሰጠው ትኩረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልል ለኢንቨስመንት እና ኢንዱስትሪው ሰፊ እድል እንዳለ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ ግብርናን ጨምሮ በክልሉ ተከማችቶ ለሚገኘው የተፈጥሮ ሀብት ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ነው የገለፁት።
የክልሉን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ከሚሰሩ ሥራዎች በተጨማሪ እንደ ውሀ የንግድ ሥረዓት እና ማሽን ያሉ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በተያዘው የበጀት ዓመት 280 አነስተኛ የውሀ ማቆርያዎችን ለመገንባት ታቅዶ እስካሁን 73 ያክሉ መገንባቱን አንስተው የንግድ ሥርዓቱን ለማስተካከል እንደ ኦሮ ፍሬሽ ያሉ የገበያ ትስስሮች መፈጠራቸውም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ የገለፁት።

በአጠቃላይ ለግብርናው ዘርፍ የተሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ በማስቀጠል እና በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ወደ ልማት ለመቀየር በጋራ እንደሚሰራ አንስተዋል።

በተለይም የክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተነቃቃ ሁኔታ ላይ በመኖሩ በእድሉ መጠቀም የሚፈልጉ አካላት ወደ ክልሉ እንዲመጡ ጥሪ ቀርቧል።

በሚልኪያስ አዱኛ