5 ከባድ የብሬን መሳሪያዎችን በሕገወጥ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ ተያዘ

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) 5 ከባድ የብሬን ጦር መሳሪያዎችን ከደሴ ወደ ምስራቅ ሐረርጌ ዞን በሕገወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።

ግለሰቡ የተያዘው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባደረገው ክትትል እንደሆነ ተነግሯል።

ግለሰቡ ሰሌዳ ቁጥሩ አአ ኮድ2 B23782 በሆነ ላንድ ክሩዘር ተሽከርካሪ ላይ በድብቅ በመጫን መዳረሻውን ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሀረርጌ ዞን በማድረግ በመጓዝ ላይ እያለ በቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን ኢዜአ ዘግቧል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የመረጃ ኦፊሰሮች በግለሰቡ ላይ ከመነሻው ክትትል በማድረግ አዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 በተለምዶ ካራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርስ ለአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ጥቆማ በመስጠት ከነጦር መሳሪያው እጅ ከፍንጅ መያዙ ተገልጿል።