ኢትዮጵያ እና ቻይና በኢኮኖሚና ልማት ትብብሮች ዙሪያ ውይይት አካሄዱ

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ እና ቻይና የሁለቱ አገራትን የኢኮኖሚና ልማት ትብብሮች በተመለከተ ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም (FOCAC) ማዕቀፍ ለቻይና ወገን በቀረቡት ነባርና አዲስ ፕሮጀክቶች ዙሪያም ሰፋ ያለ ምክክር ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ወቅት በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ኢትዮጵያ በርካታ መሰረተ ልማቶችን ለማጠናቀቅ የቻይና ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው በዳካር በተካሄደው የ8ኛው የቻይና አፍሪካ የሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ በተቀመጡት ዘጠኝ ፕሮግራሞች መሰረት ኢትዮጵያ ያቀረበቻቸው አዳዲስ እና ነባር ፕሮጀክቶች ተፈጻሚ እንደሚሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ አያይዘውም እያደገ የመጣው የኢትዮጵያና ቻይና የኢኮኖሚ ልማት ትብብር የአገራቱ ግንኙነት የላቀ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላትን የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ ጤናና የዲጂታል ኢኮኖሚ ትስስር የበለጠ በማጎልበት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንደምትሰራም ተናግረዋል፡፡
በቻይና የንግድ ሚኒስቴር የምዕራብ ኤስያና አፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ጂያንግ ዌይ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን በመጠቆም በቻይና አፍሪካ የትብብር ፎረም የተቀመጡ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከኤምባሲው ጋር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ለማድረግ የሚያበረታቱ መሆኑን መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ቻይና ለኢትዮጵያ ትልቋ የንግድ እና ልማት አጋር እንዲሁም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ምንጭ መሆኗም ተጠቅሷል፡፡