ኢትዮጵያ ያላትን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ መጠን የሚያሳውቅ ጥናት እንዲደረግ ስምምነት ተፈራረመች

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ ያላትን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ መጠን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ግምገማን የሚያሳውቅ ጥናት እንዲደረግ ከአሜሪካው ኤንኤስኤአይ ኩባኒያ ጋር ስምምነት ተፈራርማለች፡፡

የማዕድን ሚኒስትር ታከለ ኡማ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “ኢትዮጵያ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተሳትፏ ከፍ እንዲል ካሰብን አሉን የምንላቸው ሀብቶቻችን በጥናት የተረጋገጠ ዓለም ዐቀፍ እውቅና ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል፡፡

ጥናቱ ኢትዮጵያ ያላት የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ለማዳበሪያና ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች ጥቅም ላይ እንዲውል የሚረዳና ለዓለም ዐቀፍ የኢንቨስትመንት ተቋማትም ስለ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሀብቷ መጠንና አይነት ማረጋገጫን የሚሰጥ እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከጥናቱ በኋላ የምገኘው ዓለም ዐቀፍ ማረጋገጫ ኢትዮጵያ በዘርፉ የምትፈልገውን ኢንቨስትመንት የመሳብና የመደራደር አቅሟን ከፍ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በፊርማ ሥነሥርዓቱ ላይ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ ጃኮብሰን ተገኝተዋል፡፡