መምሪያው የሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ ከፌዴራል እና ከክልል የጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም ውጤታማ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማበርከቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።
የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ በሕግ ማስከበርና ኅልውና እንዲሁም በኅብረ ብሔራዊ አንድነት ዘመቻ ስኬታማ የግዳጅ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አባላት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ ከፍተኛ የሰራዊቱ አመራሮች እንዲሁም የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተገኙበት እውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያ አመራሮችና ባለሙያዎች በእልህ እና በቁጭት በአነስተኛ የሰው ኃይል ቀን ከሌሊት ተግተው በመስራታቸው መከላከያ ሰራዊቱ ላስመዘገበው ድል ከፍተኛ አስዋጽኦ አበርክተዋል ብለዋል።
መምሪያው ከጤና ሚኒስቴር እና መሰል ተቋማት ጋር በትብብር መስራቱ ሰራዊቱ በጀግንነት ተዋግቶ እንዲያሸንፍ ከማስቻሉም በላይ የሰራዊቱን ሞራል በሚገነባ መልኩ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን የጠቆሙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዘመቻዎቹ ለተመዘገበው ውጤት ሁሉንም ባለድርሻዎች ማመስገናቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ሌተና ጄነራል ጥጋቡ ይልማ በሀገሪቱ ላይ የኅልውና አደጋ ተከስቶ በነበረበት ወቅት የመከላከያ ጤና ዋና መምሪያው ያለውን ውስን የሰው ሃብት በመጠቀም በውጊያው የተሳካ የጤና አገልግሎት ድጋፍ በተቀላጠፈ መንገድ መስጠት መቻሉን ገልፀዋል።