ሕዝባዊ ውይይት በመዲናዋ እየተካሄደ ነው

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) የብልፅግና ፓርቲ ሕዝባዊ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የውይይት መድረኩ ብልፅግና ፓርቲ ባካሄደው ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችና የተቀመጡ ቀጣይ አቅጣጫዎች ከሕዝብ አሁናዊ ፍላጎት አንፃር ምን ያህል ይጣጣማል በሚለው ላይ ከሕዝብ ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ ነው ተብሏል።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተቀመጡ አቅጣጫዎች የሕዝብን ወቅታዊ ችግር መሰረት ያደረጉ፣ ወቅታዊና አንገብጋቢ መሆናቸውን በመድረኩ ይፈተሻሉ ብለዋል፡፡

ውይይቱ ከሕዝብ የሚነሱ ሀሳቦችን በቀጣይ የሚተገበሩ እቅዶች ውስጥ በማካተት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና ማሳያና የአፍሪካ የከተሞች ልማት ሞዴል ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን ይህንንም ለማሳካት ሕዝብ የሚያነሳውን ጥያቄ ማድመጥ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ሕዝብን ማዳመጥና    መግባባት ላይ ያለመ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኑሮ ውድነት፣ የሰላምና መረጋጋት፣ የመልካም አስተዳደርና ብልሹ አሰራር ችግርና ሌሎችም ከመወያያ ነጥቦች መካከል ሆነዋል።

በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶችና የሕዝብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በትዕግስት ዘላለም