የብልጽግና ፓርቲ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ በባሕር ዳር እየተካሄደ ነው

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ውሳኔዎችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የሚመክር ሕዝባዊ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር)፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጸርሕፈት ኃላፊ ፍቃዱ ተሠማ፣ የባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ተገኝተዋል፡፡

ፓርቲው ፈተናዎች ሳይበግሩት የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየሠራ መሆኑን ከንቲባ ድረስ ገልፀዋል።

በተለይም የተጀመረውን አገር የማፅናት ጉዞ ለማስቀጠል ብልጽግና በጉባኤው የወሠናቸው ውሳኔዎች እና የተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ ከሕዝብ ጋር ለመምከር የተሠናዳ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል።

ርዕሠ መስተዳድር ይልቃል በብልጽግና ጉባኤ የፈተናዎች መብዛት ከጉዟችን አያስቀረንም የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው ከዚህ ሕዝባዊ ምክክር በመነሳትም የኅብረተሰቡን ቀዳሚ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በፅናትና እልህ እንሠራለን ሲሉ መናገራቸውን ኢብኮ ዘግቧል።