ክልሉ በኤክስፖርት ምርቶች የታደለ በመሆኑ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገነባ ተጠየቀ

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በገበያ ተኮርና ኤክስፖርት ምርቶች የታደለ በመሆኑ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲገነባ በቦንጋ ከተማ በተካሄደው ሕዝባዊ ውይይት ላይ የተሳተፉ አካላት ጠየቁ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ዙሪያ በቦንጋ ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ መሰረተ ልማቶችን ለማስቀጠል እና የብልጽግና ጉባኤ ያሳለፋቸውን ወሳኔዎች ለመተግበር እንደሚሠሩ በካፋ ዞን የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
ጉባኤው የኅብረተሰቡ የሠላም፣ ልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት መምከሩን ገልጸዋል።
በተለይም ኅብረተሰቡ የሠላሙ ባለቤት እንደመሆኑ ሠላም እና ልማት እንዲረጋገጥ ሁሉም የመሪነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
ክልሉ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ በመሆኑ ይህንን ሀብት አቀናጅቶና አስተባብሮ ጥቅም ላይ ለማዋል ቁርጠኛ አመራር እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የውይይት መድረኩ ችግሮቻችንን በስፋት እንድንገልጽ እድል የሰጠን በመሆኑ መልካም ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት የሕዝብን ቅሬታ መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በውይይቱ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ ለዓመታት አገልግሎት መስጠት ያልቻለው ብሔራዊ የቡና ሙዚየም፣ የመንገድ እና መሠል የመሠረተ ልማት ችግሮችን በስፋት አንስተዋል።
የብልጽግና የጉዞን ትልም ለማሳካት በአንድነትና በትብብር መንፈስ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል።