ም/ጠ/ሚ ደመቀ ኤች አር 6600 የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት ከግምት ያላስገባ ነው አሉ

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ እና ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ያላስገባ መሆኑን ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በምስራቅ አፍሪካ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ መንግሥት በትግራይ ክልል ሰብኣዊ ድርጅቶች ድጋፍ ለተጎጂዎች ያደርሱ ዘንድ አስፈላጊውን እገዛ ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።

ሰብኣዊ አቅርቦቱ ላይ በአሸባሪው ሕወሓት መስተጓጎል መፈጠሩን እና ቡድኑ በአጎራባች ክልሎች እየፈጸመ ያለውን ትንኮሳ በተመለከተም አብራርተዋል።

ኤች አር 6600 እና ኤስ 3199 ረቂቅ የአሜሪካ እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ እና ታሪካዊ ግንኙነት ከግምት ያላስገባ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

አሜሪካም በኢትዮጵያ ሰላም እና ዴሞክራሲን ከማስፈን ይልቅ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚጎዳውን ረቂቅ ታጸድቀዋለች የሚል እምነት እንደሌላቸውም አክለው ገልጸዋል።

ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የወሰዳቸውን አዎንታዊ እርምጃዎችን በተመለከተ አገራቸው እውቅና የምትሰጠው መሆኑን መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።