ሚኒስትሯ በድሬዳዋ እየተገነባ ያለውን ደረቅ ወደብ ጎበኙ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ69 ሚሊዮን 589 ሺሕ 56 ዶላር ወጪ እየተገነባ ያለውን የደረቅ ወደብ ጎብኝተዋል፡፡

የደረቅ ወደቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በተለይም የገቢና ወጪ ንግድን ለማሳለጥ ከማገዙም በላይ በጅቡቲ ወደብ ላይ ለብዙ ጊዜ ይቀመጡ የነበሩ ኮንቴይነሮች ወደዚህ እንዲቀመጡ በማድረግ ሀገሪቱ ዪታወጣውን የውጪ ምንዛሬ ወጪን ይቀንሳል ተብሏል፡፡

ደረቅ ወደቡ ደረጃውን የጠበቀ የተሸከርካሪዎችና ኮንቴይነሮች ጋራዥ እንዲሁም በባቡር የሚገቡ ኮንቴይነሮች የክብደት ሚዛን አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ በቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እየተከናወነ ሲሆን ግንባታው 95 ነጥብ 93 መድረሱን የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ከሚኒስትሯ በተጨማሪ የድሬዳዋ አሰተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊና የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሳዳት ነሻ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች በጉብኝቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።