ባለስልጣኑ 46 አገልግሎቶችን በበይነ መረብ መስጠት ጀመረ

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን 46 አገልግሎቶቹን በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችለውን ሥርዓት አስጀመረ፡፡

አገልግሎቶቹ ሙሉ ለሙሉ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የለሙ ሲሆን የኤሌክትሪክ ሥራዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት፣ እድሳት ማድረግ፣ ምትክ መስጠት፣ አዲስ ጊዜያዊና ቋሚ የኢነርጂ አገልግሎት ኩባንያ ፈቃድ መስጠት፣ ኦን ግሪድ የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ፣ ማመንጨትና ማከፋፈያ የሥራ ፈቃድ መስጠት፣ ንግድ ፍቃድ ማደስ እና ሌሎችንም የያዘ ነው ተብሏል፡፡

ዛሬ ተመርቀው ወደ ሥራ የገቡት አገልግሎቶች አጠቃላይ በበይነ መረብ የሚሰጡ የመንግሥት አገልግሎቶችን ብዛት ወደ 331 ከፍ እንዳደረገው ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በኤሌክትሮኒክ አገልግሎት ውስጥ ማነቆ የነበረውን የህግ ማዕቀፍ አለመኖር ችግር ለመቅረፍ ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባው የትራንዛክሽን አዋጅ በተጨማሪ የተለያዩ ህግና መመሪያዎች እየተዘጋጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ በመሆኑ ባለስልጣኑ የሚጠበቅብተን ኃላፊነት እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ተወካይ ዋና ዳይሬክተር ጌታሁን ሞገስ በወረቀት ሲሰጡ የነበሩ አገልግሎቶች በበይነ መረብ መሰጠታቸው የተቀላጠፈ አገልግሎት ለተገልጋዮች ለመስጠት እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡