አመራሮቹ ከተወከሉበት ክልል ውጭ ከሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር መወያየት አዲስ የፖለቲካ ባህል የሚፈጥር ነው

ሙፈሪሃት ካሚል

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ከተወከሉበት ክልል ውጭ ከሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው አብሮነትን ማጎልበት የሚያስችል አዲስ የፖለቲካ ባህል እንደሚፈጥር የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ፡፡

ሚኒስትሯ በደሴ ከተማ ከኅብረተሰቡ ጋር ያደረጉትን ሕዝባዊ ውይይት በተመለከተ ለኢዜአ በሰጡት ማብራሪያ በኢትዮጵያ ልዩነት ላይ ብቻ ትኩረት ተደርጎ ለዓመታት የተሰበከው የፖለቲካ እሳቤ በሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ መጠራጠር ማስከተሉን አንስተዋል።

በአመራሮች ዘንድም አለመተማመንን ፈጥሮ፣ አገርን ለከፋ ችግር ሲዳርግ እንደነበር የገለጹት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሏ ይህ የተሳሳተ የፖለቲካ አካሄድ ልጓም ተበጅቶለት ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዘንድሮ በብልጽግና ፓርቲ እውን ሆኗል ብለዋል።

በዚህም ብልፅግና ፓርቲ የጥላቻ ትርክቶችንና እሱን ተከትሎ የመጡ ቁርሾዎችን ለመቅረፍና አንዲት ጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ አገር ለመገንባት የሚያስችል አካሄድ ተከትሏል ነው ያሉት።

ከብልጽግና ፓርቲ ዓላማዎች መካከል አንዱ አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር ነው ያሉት ሚኒስትሯ የፓርቲው አመራሮች በአካባቢያቸው ሳይታጠሩ አንዱ የሌላውን ክልል ደስታና ሀዘን የሚጋራበት አሰራር መዘርጋቱንም አመልክተዋል፡፡

ይህም ”አገር የምንመራ ሰዎች ወሰንና ድንበር ሳያግደን ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ ችግሮችን ተረድተን፣ የመፍትሄው አካል እንድንሆን ያስችላል” ብለዋል።

”ስለአማራ ክልል ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅ የግድ ከዚያ ክልል የመጣ መሪ ብቻ መሆን የለበትም” ያሉት ሚኒስትሯ ሕዝብን የሚያገለግሉ አመራሮች በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን አኗኗርና ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

አብሮነትንና ወንድማማችነትን የሚያገለብተውን ይህን የፖለቲካ አካሄድ ማጠናከር ደግሞ የብልጽግና ፓርቲ መሰረታዊ እሳቤ መሆኑንም ተናግረዋል።

 

ለፈጣን መረጃዎች፦

ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW

ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth

ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured

ቲዊተር https://twitter.com/walta_info

አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!