በክልሉ በበጀት ዓመቱ 6 ወራት በማዕድን ዘርፍ 16 ኩባንያዎች ፈቃድ ወስደዋል

መጋቢት 15/2014 (ዋልታ) በአማራ ክልል በ2014 ዓ.ም በጀት በ6 ወራት እቅድ በማዕድን ማምረት ኢንቨስትመንት 16 ኩባንያዎች ፈቃድ መውሰዳቸውን ርዕሰ መስተዳድር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

4 በድንጋይ ከሰል 5 ደግሞ በእብነበረድና ግራናይት ለማምረት ፈቃድ የወሰዱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ ወደ ሥራ ገብተዋል።

በተመሳሳይ 7 የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ፈቃድ ወስደው ሁለቱ የግንባታ ፈቃድ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡

351 ባህላዊ ማዕድን የማምረት ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን ለ6 ሺሕ 610 ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።

የአገርን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ 7 ሺሕ 920 ኪሎ ግራም ጥሬ ኦፓልና 88 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም እሴት የተጨመረበት ኦፖል ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከ3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ተገልጿል።

በቱሪዝም ዘርፍ ባለፋት 6 ወራት ከታቀደው 20 በመቶ መፈፀም እንደተቻለም ተነግሯል፡፡

በክልሉ በዓመቱ መጨረሻ 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታስቦ በግማሽ ዓመቱ ማግኘት የተቻለው 331 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር እንደሆነም ተማለክቷል፡፡

በሌላ በኩል ጥራት ያለው ትምህርት አቅርቦትን ለማሟላት አዲስ የሥርዓተ ትምህርት ዝግጅትና ሙከራ ትግበራ በመካሄድ ላይ ነው ተብሏል።

በተለያዩ ደረጃዎች ያለፉ 134 መፅሐፍት ዝግጅት መጠናቀቁን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የግዕዝ ትምህርት ለመስጠት የአንድ ክፍል ማስተማሪያና የ4 ክፍሎች መርሃ ግብር ሥርዓተ- ትምህርት ዝግጅት መካሄዱን አብራርተዋል፡፡

ምንይሉ ደስይበለው (ከባሕር ዳር)