የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ጉዳይ የከፍተኛ የፖለቲካ አመራር ውሳኔ እንደሚያስፈልገው ተጠቆመ

መጋቢት 16/2014 (ዋልታ) ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ጉዳይ ለመፍታት የከፍተኛ ፖለቲካ አመራሩ ውሳኔ እንደሚያስፈልገው የአማራ ክልል የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ፡፡

የአማራ ክልል 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ 2ኛ ቀኑን የከሰዓት ውሎ በምክር ቤቱ አባላት ለተጠየቁ ጥያቄዎች ምላሽ እየተሰጠ ነው።

ትምህርት፣ ግብርና፣ ሥራ ፈጠራና ኑሮ ውድነትን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በክልሉ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ እየተሰጠባቸው ይገኛል።

በትምህርት ዘርፉ በተለይም የ12ኛ ክፍል ውጤት ከተጠበቀው በላይ መሆኑ ተማሪዎችን፣ የተማሪ ወላጆችን፣ መምህራርንና የትምህርት ማኅበረሰቡን ጎድቷል ተብሏል፡፡

ተማሪዎች በጦርነቱ ውስጥ ስለቆዩ በሥነ-ልቦና ለፈተናው ዝግጁ ባለመሆናቸውና በጦርነት ውስጥ ሆነው ስለተፈተኑ ተማሪዎች ውጤቱ ዝቅተኛ ሆኗልም ነው የተባለው፡፡

በዚህም የሥራ ኃላፊዎቹ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጠው ምላሽ የተማሪዎቹን ጉዳይ ለመፍታት የከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ ውሳኔ ያስፈልገዋል በሚል ምላሽ ሰጥቷል።

በሥራ ዕድል ፈጠራ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ባለፉት ዓመታት በብድር የተወሰደ በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ መመለስ ባለመቻሉ ብድር አቅራቢው የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) ማበደር አለመቻሉ ተገልጿል።

ምክንያቱም ከ3 በመቶ በላይ የብድር ብልሽት ካለ ተቋማት እንዳያበድሩ በብሔራዊ ባንክ ስለተከለከለ ወጣቶችን ተጠቀሚ ማድረግ አልተቻለም ተብሏል።

በግብርናው ዘርፍ በተለይ በግብዓት አቅርቦት ባለፈው ዓመት 6 ሚሊየን ኩንታል መቅረቡ ተጠቁሟል፡፡
በዚህ ዓመት 8 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ያስፈልጋል የተባለ ሲሆን ነገር ግን ክልሉ አሁን 1 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ እንዳለው ነው የተገለጸው።

የበጋ ስንዴ በተመለከተ ከ40 ሺሕ በላይ ሄክታር መሸፈን እንደተቻለና ለዚህም የክልሉ መንግሥት 30 ሺሕ ኩንታል የምርጥ ዘር ስንዴ በማቅረብ ከፍተኛ ሥራ መስራቱ ተገልጿል።

የግብርና ሥራን ውጤታማ ለማድረግ የተፈጥሮ ማዳብሪያ ማዘጋጀት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ እንዲሁም ክልሉ ካለው የተፈጥሮ ሀብትና መሬት ጋር ያገናዘበ የእርሻ ሥራ መስራት እንደሚገባ በተሰጠው ምላሽ ተጠቁሟል፡፡

የዋጋ ግሽበቱ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ሲነፃፀር በክልሉ ያለው ከፍተኛ ነው የተባለ ሲሆን ለዚህ ደግሞ የምርት እጥረት፣ ሰው ሰራሽ የምርት እቀባ እና ወቅታዊ የዓለም ዐቀፍ ሁኔታው ለኑሮ ውድነቱ አስተዋፅኦ አድሮጓል ተብሏል።

ሌላው ለኑሮ ውድነቱ ምክንያት የትርፍ ህግ የሚወስን ህግ ባለመኖሩ በነፃ ገበያ ሰበብ ገበያው እንዲንር አድርጓል ነው የተባለው።

የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል በክልሉ ንግድ ቢሮ የእሁድ ገበያ ማስጀመር፣ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲያገኙ በማድረግ ህገወጥ ንግድን የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ ነው ተብሏል።

ምንይሉ ደስይበለው (ከባሕር ዳር)