ለደኅንነት አገልግሎት የሚገጠሙ ካሜራዎችን የሰረቁና የገዙ ግለሰቦች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ

መጋቢት 16/2014 (ዋልታ) በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ከሚገኘው ሲ.ጀ.ሲ.ኦ.ሲ ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ 996 ሺሕ ብር የሚያወጡ 41 ለደኅንነት አገልግሎት የሚውሉ ካሜራዎችን እና 36 የካሜራ መደገፊያዎችን የሰረቁት ተጠርጣሪዎች በ41 ሺሕ ብር ከገዙ ሁለት ተቀባይ ግለሰቦች ጋር ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የስርቆት ወንጀሉን የፈፀሙት ሁለት ግለሰቦች ከዚህ ቀደም በድርጅቱ ውስጥ በቀን ሰራተኝነት ሲሰሩ እንደነበር የገለጸው ፖሊስ የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ/ም ወንጀሉን እንደፈፀሙ በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ግለሰቦቹ ወንጀሉን በፈጸሙ በአስረኛው ቀን ድርጅቱ ንብረቶቹ መሰረቁን ተገንዝቦ ለፖሊስ ሪፖርት አድርጎል።
የወንጀሉ ሪፖርት በደረሰው በሦስተኛው ቀን ተጠርጣሪዎቹን ይዞ ንብረቶቹን በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ሮባ ዳቦ ቤት አካባቢ ከሚገኙ ከሁለት ግለሰቦች አስመልሶ ምርመራውን መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጨምሮ ገልጸዋል።