በመዲናዋ የተሰረቁ የተለያዩ እቃዎችን እየተቀበሉ በሚሸጡ የንግድ ሱቆች ላይ እርምጃ ተወሰደ

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) በመዲናዋ የተሰረቁ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስና የመኪና መለዋወጫ እቃዎችን በሚቀበሉ የንግድ ሱቆች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ፖሊስ እንዳስታወቀው በልደታና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች የተሰረቁ እቃዎችን በመግዛት የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን የንብረቶቹ ማከማቻ የነበሩ ሱቆች ላይም እርምጃ ተወስዷል።

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት፣ አራት እና ወረዳ ሰባት አካባቢ አንዳንድ ሱቆች በስርቆት የሚመጡ የተለያዩ እቃዎችን እንደሚቀበሉ ተደርሶባቸዋል።

በመሆኑም ፖሊስ በክፍለ ከተማው መጋቢት 15 እና 16 ቀን 2014 ዓ.ም በተለያዩ ሱቆች ላይ ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የተሰረቁ የሞባይል ስልኮች፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እና የተሽከርካሪ መለዋወጫዎችን ይዟል።

በዚህም 80 የሞባይል ስልኮች፣ 24 ሲም ካርዶች፣ ሁለት ላፕቶፕ፣ አንድ ህገ-ወጥ ሽጉጥ እና በርካታ የመኪና መለዋወጫ እቃዎች ተይዘዋል።

ከተያዙት እቃዎች ጋር 11 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመልክቷል።

በተመሳሳይም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በንግድ ሱቆች ላይ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ 618 የሞባይል ስልኮች፣ አምስት ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ 45 ሲም ካርዶች እና ሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ተይዘዋል።

ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ይገኛል ተብሏል፡፡