ብልፅግና ፓርቲ ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የሚመልሱ እቅዶች ተዘጋጅተው እንዲተገበሩ አቅጣጫ አስቀመጠ

መጋቢት 19/2014 (ዋልታ) በመላ አገሪቱ በተካሄዱ ውይይቶች ሕዝቡ ያነሳቸውን ጥያቄዎች የሚመልሱ እቅዶች ተዘጋጅተው እንዲተገበሩ የብልፅግና ፓርቲ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ፓርቲው በቅርቡ ባካሄደው አንደኛ ጉባዔው ያሳለፋቸውን ውሳኔዎችና ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች አስመልክቶ በመላ አገሪቱ ከሕዝቡ ጋር ሲያደርግ የነበረውን ውይይት አጠናቋል፡፡
የውይይቶቹን መጠናቀቅ ተከትሎም በዛሬው እለት በማእከል ደረጃ በመድረኮቹ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በተገኙበትና የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በመሩት የዛሬው መድረክ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደር መድረኮች የተነሱ ዋና ዋና ሃሳቦች ተገምግመዋል፡፡
በመድረኩ በሕዝቡ የተነሱትን የሕዝብ ጥያቄዎች ለመመለስና ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ዝርዝር እቅዶች ተዘጋጅተው እንዲተገበሩ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በመሆኑም በአጭር ጊዜ ውስጥ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶች ተዘጋጅተው ወደ ተግባር እንዲገባ ፓርቲው አቅጣጫ ማስቀመጡን ከፓርቲው ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡