በባሕር ትራንስፖርት ላይ ለተፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ ነው

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በባሕር ትራንስፖርትና የገቢ እቃዎች ማጓጓዝ ላይ ለተፈጠረው ጫና አማራጮች እየተፈለጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ገለጸ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረው ጫና በማገገም ላይ የነበረው የዓለም የንግድ መዛባት በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለሌላ ቀውስ ተዳርጓል።
በተለይም የምግብ፣ የነዳጅ፣ የምግብ ዘይትና ሌሎችም ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ታይቶባቸዋል።
የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በተለይም የባሕር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ማስከተሉ እየተነገረ ይገኛል።
በድርጅቱ የባሕር ትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ወንድወሰን ካሳ የሁለቱ አገራት ጦርነት በዘርፉ ላይ ከባድ ፈተና መደቀኑን ገልጸው የኢትዮጵያ መርከቦች የአገልግሎት ወጪ እየጨመረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በተለይም የነዳጅ ወጪያቸው ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ የ42 በመቶ ጭማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል።
የጦርነቱ ተፋላሚ አገራት የአውሮፓና የእስያ መተላለፊያ በመሆናቸው በተለይም በባቡር ለሚጓጓዙ ምርቶች ከፍተኛ ችግር ሆኗል ብለዋል።
በፈረንጆቹ 2021 እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኮንቴይነሮች በባቡር መጓጓዛቸውን እና በዚህ ዓመት የሚቋረጥ ከሆነ ከ5 እስከ 8 በመቶ እቃዎች ወደ ባሕር ትራንስፖርት ሊመጡና ጫና ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ገልጸዋል።
ጦርነቱ እልባት ካላገኘ በባሕር ትራንስፖርቱ ላይ የሚፈጥረው ጫና ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችልም ተናግረዋል።
የወደቦችና የባሕር ትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች ሊወድሙ ስለሚችሉ ወደ ተለመደው እንቅስቃሴ በፍጥነት መግባት ሊያስቸግር እንደሚችል መጠቆማቸውን የኢዜአ ዘገባ አመልክቷል።
በመሆኑም የባሕር ትራንስፖርቱ አሁን ካለበት ጫና ይበልጥ ወደ ከፋ ችግር እንዳይሸጋገር ለሚገቡ ምርቶች አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ይገባል ብለዋል።
ከጥቁር ባሕር አካባቢ የሚገቡ ምርቶችን የሚተኩ አማራጮች በሌሎች አገራት መኖራቸውን የተናገሩት ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ከኦማን የብረት ምርት በማስገባት ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
ከህንድም የብረትና ስንዴ ምርት አማራጭ መኖሩን ጠቅሰው ካናዳና አርጀንቲናም የስንዴ አምራች በመሆናቸው አማራጮችን ማየት ይጠቅማል ብለዋል።
የሱፍ ዘይት በጦርነቱ ምክንያት ምርቱ ወደ ገበያ ባይቀርብም ከኢንዶኔዥያና ማሌዥያ የፓልም ዘይትንና በተወሰነ ደረጃም የሱፍ ዘይትን ማስገባት ይቻላል ብለዋል።