አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በጋሞ ዞን የሚገኙ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ መስህቦችን ጎበኙ

መጋቢት 20/2014 (ዋልታ) የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በጋሞ ዞን የሚገኙ ተፈጥሮአዊና ባህላዊ መስህቦችን እንዲሁም ከአርባ በላይ ምንጮችና የተለያዩ እፅዋቶች የሚገኙበትን የአርባምንጭ የተፈጥሮ ደን ጎብኝተዋል።

በዞኑ ከሚገኙ መስህቦች መካከል አንዱ የሆነው እና በ1967 ዓ.ም የተመሰረተው የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ፤ ተ 91 የአዕዋፍ እንዲሁም 351 የአጥቢ እንስሳት ዝሪያ በውስጡ መያዙን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ ሽመልስ ዘነበ በጉብኝቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡

የቤት እንስሳት ወደ ፓርኩ መግባት፣ መጤ ወራሪ አረም፣ እንጨት ለቀማ፣ ደለል፣ የመንገድ ችግር እና የእሳት አደጋ የፓርኩን ህልውና እየፈተኑ የሚገኙ ችግሮች መሆናቸውንም ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

አምባሳደር ናሲሴ በበኩላቸው የተጠቀሱ ችግሮች በፕሮጀክት መልክ ለሚኒስቴሩ ቀርበው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በጉብኝታቸውም በጋሞ ባህላዊ መንደር፤ ከቀርከሃ ብቻ የሚሰራው እና ከ90 ዓመታት በላይ የሚቆየውን የጋሞ ባህላዊ ጎጆ፣ የባህላዊ ምግቦችና መጠጦች አዘገጃጀትን፣ ከአካባቢ እጽዋት የሚዘጋጁ መዋቢያዎችን፣ የጥጥ ፈትል፣ ሽመና፣ የጋሞ ባህላዊ ሙዚቃዎችና ጭፈራዎችን መመልከታቸውን የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።