የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሥራ ለአካባቢው ኅብረተሰብና ለአገር ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ዳውሮ ዞን የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ማዕድን ሥራ ለአካባቢው ኅብረተሰብ ብሎም ለአገር ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ተገለጸ።

በዳውሮ ዞን ጎዓ የማዕድን ቁፋሮ ዋና ሥራ አስኪያጅና ባለቤት ደረጀ ወንድሙ እንደገለጹት ከድንጋይ ከሰል ምርት ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የአካባቢውን ማኅበረሰብ የኢኮኖሚ ችግር ይቀርፋል።

ለድንጋይ ከሰል ምርት የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ 5 ነጥብ 1 ኪ.ሜ የመንገድ ሥራ በመስራት የአካባቢውንም ኅብረተሰብ እየጠቀመ እንዳለ ተናግረዋል።

ድርጅቱ በቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ 20 የአካባቢ ወጣቶችን በቋሚነት ወደ ሥራ ያስገባ ሲሆን በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ሲገባ በርካታ ወጣቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አንስተዋል።

የዳውሮ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ምክትል ኃላፊና የንጹህ መጠጥ ውሃ ዘርፍ ኃላፊ ስንታየሁ መኩሪያ በዘርፉ ከተለያዩ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው ወደ ሥራ ያልገቡ ወጣቶችን በማደራጀት የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው እየተሰራ እንደሆነ መግለፃቸውን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ አመላክቷል።