ሩሲያ እና ዩክሬን በቱርክ ያደረጉት ውይይት ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውይይቶች የተሻለ እንደሆነ ተጠቆመ

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) ሩሲያ እና ዩክሬን በቱርክ ኢስታምቡል ያደረጉት ውይይት ተስፋ የተጣለበት እና ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውይይቶች የተሻለ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
35ኛ ቀኑን የያዘው የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ለማስቆም ተደጋጋሚ ውይይቶች ሲካሄዱ ቢቆዩም ፍሬ ሳያፈሩ በመቅረታቸው በሀገራቱ ጦርነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
ትላንት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል በቱርክ ኢስታንቡል በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ውይይት ሩሲያ በኪየቭ እና በቼርኒሂቭ አካባቢ የምታደርገውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ ለመቀነስ ቃል መግባቷ ተገልጿል፡፡
ይሁንና የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪም ሆኑ የሌሎች ሀገራት መሪዎች ሩሲያ ይህንን መወሰኗን በቀላሉ ሊቀበሉት እንዳልቻሉ ተነግሯል፡፡
ሩሲያ ለሰላም ለሚደረገው ድርድር ‹‹የጋራ መተማመንን ለማሳደግ›› በሁለቱ ቁልፍ የዩክሬን አካባቢዎች የሚካሄደውን ወታደራዊ ውጊያ እንደምትቀንስ አስታውቃለች፡፡
በዋና ከተማዋ ኪየቭ እና በሰሜናዊቷ የቼርኒሂቭ ከተማ ዙሪያ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለመቀነስ መወሰኑ ከውይይቱ የተገኘ የመጀመሪያው ተጨባጭ እድገት ማሳያ ነው ቢባልም የትኛውንም ወታደራዊ እንቅስቃሴ መቀነስ ምን ያህል እንደሆነ ግልፅ አይደለምና ዩክሬን በሩሲያ ውሳኔ ላይ አሁንም ተጠራጣሪ ነች ተብሏል።
አሜሪካ እና እንግሊዝም የተገባው ቃል በጥንቃቄ መያዝ አለበት ሲሉ ፕሬዝዳንት ዘለንስኪም ሩሲያ ለገባችው ቃል ምላሽ ሲሰጡ ‹‹ዩክሬናዊያን የዋህ አይደሉም የሩሲያን ቃል አምነው የሚቀበሉት›› ብለዋል።
ተጠራጣሪው ዘሌንስኪ “ምልክቶቹ አዎንታዊ ናቸው ማለት እንችላለን ነገር ግን እነዚያ አዎንታዊ ምልክቶቹ ግን የምናያቸውን ፍንዳታዎችና የሩሲያን ወታደራዊ እርምጃዎች አይደብቁም ብለዋል፡፡ ሌሎችም አገራትም በጉዳዩ ላይ በጥንቃቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ‹‹ድርጊታቸው ምን እንደሆነ እስካላየሁ ድረስ ያነበብኩትን ውሳኔ አላምንም›› ብለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው ሩሲያ በምትናገረው እና በምታደርገው መካከል ልዩነት አለ ሲሉ ተደምጠዋል።
ከእንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ጣሊያን የተውጣጡ መሪዎችም ምዕራባዊያን አገራት በሩሲያ ላይ የሚያደርጉትን ጥበቃ እንዳያቋርጡ አሳስበዋል።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ጽሕፈት ቤት እንደገለፀው ‹‹በዩክሬን ላይ እየደረሰ ያለው አሰቃቂ ሁኔታ እስካልተጠናቀቀ ድረስ የምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ውሳኔ መዘናጋት እንደማይቻል ተስማምተዋል›› ብለዋል፡፡
የፔንታጎን ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ሩሲያ ይህን ትበል እንጂ ‹‹በሌሎች የዩክሬን አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥቃትን እንደምትፈጽም ለመከታተል ዝግጁ ሁኑ›› ሲሉ ብለዋል፡፡
የእንግሊዝ የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ሩሲያ ‹‹ጦርነቱን ከሰሜን ወደ ምስራቅ በዶኔትስክ እና በሉሃንስክ ክልሎች ልትቀይረው ትችላለች››ሲል አስጠንቅቋል።
የሩሲያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር አሌክሳንደር ፎሚን ለሞስኮ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች በሆኑት የዩክሬን ‹‹ገለልተኛነት እና የኒውክሌር-አልባነት ሁኔታ›› ላይ መሻሻል ታይቷል ብለዋል።
በቱርክ ኢስታንቡል እየተካሄደ ያለው ድርድር በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታትም ይቀጥላል ያሉት የፕሬዝዳንት ዘሌኒስኪ አማካሪ የዩክሬን ተደራዳሪዎች በስምምነቱ ላይ ሕዝበ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ በመጠቆም ሀገራቸው የደኅንነት ዋስትና የምታገኝ ከሆነ ገለልተኛ ለመሆን እንደምትስማማም ገልፀዋል፡፡
የክሬሚያ ጉዳይ ለብቻው እንደሚታይ ገልጸው ቱርክን ጨምሮ ለወደፊት ሰላማችን ዋስትና ናቸው ያሏቸውን ስምንት ሀገራት ዘርዝረው አስቀምጠዋል፡፡
የሩሲያ ተደራዳሪዎች በበኩላቸው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ዜሌንስኪ በረቂቅ የስምምነት ሃሳቡ ላይ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ በግንባር ሊገናኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ ይህንንም የሁለቱም ሀገራት ተደራዳሪዎች በሰጡት መግለጫ ጠቅሰውታል፡፡
ሆኖም መሪዎቹ የሚገናኙት ተደራዳሪዎቹ በሚያዘጋጁት ረቂቅ የስምምነት ሃሳብ ላይ ከተስማሙ እና በሀገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከተፈረመ በኋላ ነው፡፡
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ በበኩላቸው ድርድሩ ተስፋ ሰጭ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
በዚህ መካከል ግን ጦርነቱ አሁንም ቀጥሏል፤ የዩክሬን ወታደሮችም በሩሲያ ጦር የተያዙ የኪየቭ መሬቶችን መልሶ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ውጊያ በማካሄድ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
በትዕግሥት ዘላለም