ኢትዮጵያ በ8ኛው የበርሊን የኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው

መጋቢት 21/2014 (ዋልታ) በ8ኛው የበርሊን የኢነርጂ ሽግግር ጉባኤ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ኢትዮጵያን ወክለው እየተሳተፉ ነው፡፡

‘ከምኞት ወደ ተግባር’ በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ የ50 አገራት የኢነርጂ ሚኒስትሮች እየተሳተፉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ከአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ የ10 አገራት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሮች እየተሳተፉ ሲሆን ጉባኤው ዘንድሮ ታዳጊ አገራት ለዜጎቻቸው ኢነርጂ ለማቅረብ ያላቸውን ህልም ወደ ተግባር እንዲቀይሩ እና ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚመከርበት እንደሆነም ተመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ ባላት የሕዝብ ቁጥር መሰረት ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት በመኖሩ ይህም በኢነርጂ ልማት ለሚሰማሩ ዓለም ዐቀፍ ኢንቨስተሮች ሰፊ የገበያ እድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ ያካሄደችው የኢነርጂ ሴክተር ሪፎርም፣ ታዳሽ ወይንም ከብክለት የጸዳ ኃይልን ለማጎልበት ያላት ቁርጠኝነት፣ ምስራቅ አፈሪካን በኃይል ለማስተሳሰር እየሰራች ያለውን ሥራ መሰረት በማድረግ በዚህ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ ላይ ተሞክሮዋን እንድታቀርብ ተጋብዛለች፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሃብታሙ ኢተፋም (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ማካፈላቸውን ከውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡