በኦዲት ምርመራ በሚጋለጡ የሰነድ ማጭበርበሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር እየተሰራ ነው

መጋቢት 22/2014 (ዋልታ) በኦዲት ምርመራ ወቅት በሚጋለጡ የሰነድ ማጭበርበሮችና ሌብነቶች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ከፖለቲካ አመራሩ ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አስታወቀ።
መሥሪያ ቤቱ በዋናነት በፋይናንሽያልና በክዋኔ የኦዲት አይነቶች ላይ የኦዲት ምርመራ እንደሚያካሂድ ይታወቃል።
በተቋሙ የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር መሠረት ደምሴ በኦዲት ሪፖርት የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ “መስሪያ ቤቱ በሚያስቀምጠው የእርምት አቅጣጫ መሠረት ተቋማት የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛል” ብለዋል።
የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ የመሻሻያ እርምጃ ከወሰዱ ተቋማት መካከል የልማት ባንክን ለአብነት ያነሱት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ተቋማቱ ከሚወስዱት ማሻሻያ ባለፈ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመቅረብ ግምገማ እንሚካሄድባቸውና የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት በሁለት የፋናንሽያልና በአምስት የክዋኔ ኦዲት ላይ ከመንግሥት ወጭ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር ግልጽ ሕዝባዊ ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል፡፡
በአንጻሩ አንዳንድ ተቋማት የተሰጣቸውን ሪፖርት ሳይፈትሹ በመቅረት ሪፖርት በሚያቀርቡበት ጊዜ ብቻ እንደሚያዩም አመልክተዋል።
የተለያዩ የሰነድ ማጭበርበሮችና ስርቆቶችን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ጥቆማ የመስጠትና እርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በዚህ ረገድ ጥሩ ጅምሮች አሉ ያሉት ኃላፊዋ የፖለቲካ አመራሩ ትኩረት ከሰጠው የኛም ሥራ ውጤታማ ይሆናል ብለዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የሚያስችል የነጠላ ኦዲት መመሪያ ማጽደቁ ይታወሳል።