ከበልግ ዝናብ 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት መታቀዱ ተገለጸ

ኢሳያስ ለማ

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በልግ ዝናብ ብቻ 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክተር ኢሳያስ ለማ በአገር ዐቀፍ ደረጃ 202 ሚለዮን ሄክታር መሬት የበልግ ዝናብን በመጠቀም እንደሚታረስ ገልጸው በዚህም 46 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ታቀዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የበልግ ዝናብ በከፍተኛ ሁኔታ እየጣለ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ቀደም ብሎም የበልግ ዝናብን በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል የበልግ ዝናብን ማልማት በሚችሉ የደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች ስልጠናዎች ተሰጥተዋል ነው ያሉት፡፡

በአገሪቱ የበልግ ዝናብን ለመጠቀም አመቺና ወሳኝ በሆኑት የደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ በኦሮሚያና ሌሎች ክልሎችና አካባቢዎች የእርሻ ሥራዎች መጀመራቸውንም አመልክተዋል።

ዝናቡን በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የተናገሩት የሰብል ልማት ዳይሬክተሩ የደቡብ እና የደቡብ ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች በዋናነት የበልግ ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች በመሆናቸው፣ አካባቢዎች በዓመት ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ውሃ የሚያገኙት በበልግ ወቅት በመሆኑ አጋጣሚውን በአግባቡ ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።

እንደኢፕድ ዘገባ እስካሁን ድረስም በልግ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት መታረሱንና 200 ሺሕ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር መሸፈኑን ተናግረዋል።

በዚህም የበቆሎ፣ የማሽላና የጥራጥሬ ዘሮች፣ የስራስር እና እንሰት መሰል ተክሎችም እንደሚዘሩ ጠቁመዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW