የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል ተጠቆመ

ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር)

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ብቃት ያለውና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት እንደሚያስችል የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትምህርት ሚኒስቴር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች ጋር በመውጫ ፈተና አሰጣጥ ዙሪያ አውደ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡

በአውደ ጥናቱ ላይ የመውጫ ፈተናን አስመልክቶ በተለያዩ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር ደኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በቀጣይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጡ የመውጫ ፈተናዎች ተገቢውን እውቀት ክህሎትና ሰብዕና ያሟላ ምሩቅ ለማፍራት እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡

መውጫ ፈተናው በምሩቃን ፕሮፋይል መሰረት ብቁና ተወዳዳሪ ምሩቃንን በማውጣት ጥራት ያለውና በአግባቡ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለገበያው ለማቅረብ እንደሚያስችል መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የመውጫ ፈተናው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ አቅማቸው እስኪጎለብትና አካዳሚክ እና ተቋማዊ ነጻነታቸው ሙሉ በሙሉ እስኪረጋገጥ ድረሰም ፈተናው በጊዜያዊነት በትምህርት ሚኒስቴር እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የመውጫ ፈተናው ከመጪው ዓመት ጀምሮ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እንደሚሰጥ እና ለዚህም ተገቢው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ታውቋል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW