የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተጨፈጨፉባቸው የጅምላ መቃብሮች ተገኙ

መጋቢት 26/2014 (ዋልታ) የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተጨፈጨፉባቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ከ1975 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች ላይ የዘር ፍጅት የፈጸመበት “ሀለዋ ወያነ” በመባል የሚታወቁ የጅምላ እስር እና የጅምላ ቀብር የሚፈጸምባቸው ቦታዎች ናቸው ተብሏል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን “ገሃነም” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኙ በርካታ የሽብር ቡድኑ የጉድጓድና የዋሻ ድብቅ እስር ቤቶች ጥናት ሲያደርግ ቆይቶ ከተጠቆሙት የጅምላ መቃብሮች መካከል ለሙከራ አምስቱን አስቆፍሮ ጭካኔ በተሞላበት ግፍ የተረሸኑ ንጹሃንን አፅም አስወጥቷል።

አካባቢውን የጀርመኑ ናዚ እስራኤላዊያንን ከጨፈጨፈበት “ኦሽዊዝ” የተባለ ማጎሪያ ጋር አነጻጽረው “የኢትዮጵያዊው ኦሽዊዝ” ሲሉ የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ቡድን አባላት “ገሃነም” በተባለው የሽብር ቡድኑ የድብቅ እስር ቤት በርካታ ሺሕ ንጹሃን ማለቃቸውን በወቅቱ በእስር ላይ የነበሩና ከሞት የተረፉ የወራሪ ቡድኑ የጥቃት ሰለባዎችን ዋቢ  አድርገው  አጥኚዎቹ መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።