በመኪና አደጋ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ

መጋቢት 27/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ሽሮሜዳ እንጦጦ አምባ ትምህርት ቤት አጠገብ በደረሰ የመኪና አደጋ የስድስት ሰዎች ህይወት አለፈ፡፡
አደጋው ከጠዋቱ 1:30 አካባቢ ከቁስቋም ወደ ሽሮሜዳ እየተጓዘ የሚገኘው ኮድ 3 A02166 ሚኒባስ ተሽከርካሪ መንገድ ስቶ በመገልበጡ እንደተከሰተ ተጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ ምርመራ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ስጦታው ወልዴ ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደገለፁት በአደጋው አራት ተማሪዎችን ጨምሮ ሁለት እግረኞች ህይወታቸው አልፏል፡፡
በተጨማሪም ሌሎች ስድስት ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ህክምና እያደረጉ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ በቦታው ተገኝተው የነፍስ አድን ሥራን ያከናወነ ሲሆን በአሁኑ ሰዓትም የአደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ይገኛል፡፡
በሀብታሙ ገደቤ