21 ከመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በአቅርቦት ሂደት ብክነት እንደሚከሰት ተገለፀ

መጋቢት 28/2014 (ዋልታ) በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ሂደት 21 ከመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ብክነት እንደሚከሰት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዘመናዊ የኃይል አስተዳደር እንዲኖር የዲጂታል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
የኤሌክትሪክ አቅርቦት እና ስርጭትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ መቆጣጠርና ማስተዳደር በሚቻለበት ሁኔታ ላይ “ዲጂታል ኤሌክትሪክ እና ኢነርጂ” በሚል ውይይት ተካሂዷል፡፡
በበይነ መረብ በተካሄደው ውይይት ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን እያስፋፋች ቢሆንም አቅርቦቱ፣ ስርጭቱና ቁጥጥሩ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አለመደገፉ ተነስቷል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ ያለኤሌክትሪክ አቅርቦት የምጣኔ ሃብት ልማት ሊታሰብ እንደማይችል ገልጸው ታማኝና ደንበኛ ተኮር አገልግሎት ለመስጠት የዲጂታል የኃይል አስተዳደር ለመዘርጋት ይሰራል ብለዋል፡፡
በዲጂታል አሰራር የተደገፈ የኃይል አቅርቦት፣ ብልሽት ከማጋጠሙ በፊት ቁጥጥር ለማድረግ፣ ጥገና ሲያስፈልግ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት እና ብክነትን ለመቆጣጠር ይረዳል ተብሏል፡፡
በውይይቱ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተውጣጡ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!