በጦርነቱና ድርቅ የተጎዱ ከ11 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ይሻሉ

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ በነበረው ጦርነትና ድርቅ ምክንያት ተጎጂ የሆኑ ከ11 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም ገለጸ፡፡
እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር በመጨመሩ ለጋሽ ሀገራት የሚያደርጉትን የሰብዓዊ ድጋፍ በእጥፍ እንዲያሳድጉም ጥሪ ቀርቧል።
የድርጅቱ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ተወካይ ሜተክ ማጅ በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት እና በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በርካታ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በጦርነቱና በድርቁ ተጎጂ የሆኑ ከ11 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊያን እና ከ700 ሺሕ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች አሁን ላይ የለጋሾችን አስቸኳይ ድጋፍ ይፈልጋሉ ብለዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም ለእነዚህ ተጎጂዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ከ600 ሚሊየን ዶላር በላይ ያስፈልገዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሰብዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን በማንሳት እስከ ፈረንጅቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ የሰብዓዊ እርዳታ የሚፈልጉ ተጎጂዎች ቁጥር በትንሹ 20 ሚሊዮን እንደሚሆን ይገመታል ብለዋል።
የተረጂዎች ቁጥር በማሻቀቡ ምክንያት የዓለም የምግብ ፕሮግራም በሶማሌ ክልል ለእያንዳንዱ ተረጂ ሲሰጥ የነበረውን የ15 ኪሎ ግራም ወርሃዊ የጥራጥሬ ድጋፍ ወደ 12 ኪሎ ግራም መቀነሱን ጠቅሰዋል።
ላለፉት ሦስት ተከታታይ ወራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ስደተኞች የሚሰጠው የምግብ ድጎማ ከ18 በመቶ ወደ 16 በመቶ መቀነሱንም አክለዋል።
ድርጅቱ በአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልሎች ለ3 ነጥብ 4 ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል ለሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ባጋጠመው ድርቅ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች ተጎጂ መሆናቸውን ጠቁመው ከነዚህ ውስጥ ላለፉት ወራት ለ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ተጎጂዎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍን ለማጠናከር የወሰደው የግጭት ማቆም ውሳኔንም ማድነቃቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከግጭት ማቆም ውሳኔ በኋላ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 20 ተሽከርካሪዎችና አንድ ነዳጅ የጫነ ቦቴ ትግራይ ክልል መግባታቸውን ተናግረዋል።
ሌሎች ተጨማሪ 35 ተሽከርካሪዎችም የአፋር ክልል ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በጦርነቱ በተጎዱ የአማራና የአፋር ክልል ዞኖች ውስጥ ባደረገው የምግብ ዋስትና ዳሰሳ በአካባቢው ከሚኖሩት 98 በመቶ ያህሉ ለከፋ የምግብ ዋስትና ችግር መዳረጋቸውን አረጋግጠናል ነው ያሉት።