በመጠለያ ጣቢያ ለ193 ሺሕ ዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ነው

ሚያዝያ 1/2014 (ዋልታ) በአፋር እና አማራ ክልሎች በመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ 193 ሺሕ ዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ማግኘታቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በሰጡት መግለጫ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ በሚያርገው ጥረት በአማራ ክልል 130 ሺሕ በአፋር ክልል ደግሞ 63 ሺሕ የሚጠጉ በመጠለያ ካምፕ የሚገኙ ዜጎች መሠረታዊ የጤና እና የሥርዓተ-ምግብ አገልግሎት ማግኘታቸው ገልጿል።

በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለወረርሽኝ፣ ለምግብ እጥረት እና ለሌሎች የጤና እክሎች እንዳይጋለጡ ጊዜያዊ የጤና ተቋማት ተሰናድተው አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመላክቷል።

በሶማሌ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችም ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲያገኙ ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎት ተደራሽ እንዲሆን ከዓለም የጤና ድርጅት እና ከዩኒሴፍ ጋር በመሆን አስፈላጊ መድኃኒቶች እንዲቀርቡ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል።

የተወሰኑ ዓለም ዐቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የድጋፍ እጃቸውን እየሰበሰቡ መሆኑ በሥራው ላይ ጫና ማሳደሩን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ አሁን ድረስ የፀጥታ ችግር ባለባቸው የአማራ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል የተወሰኑ አካባቢዎች የጤና አገልግሎትን ማዳረስ እንዳልተቻለ አስታውቋል።

በአሳንቲ ሀሰን