ከ108 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

ሚያዝያ 3/2014 (ዋልታ) ከ108 ሚሊዮን 214 ሺሕ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የገቢና የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጉምሩክ ኮምሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ሳምንት ባደረገው ክትትል 99 ሚሊዮን 386 ሺሕ ብር የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የወጭ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች መያዙን ነው የገለጸው፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ ኤርፖርት እና ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 36 ነጥብ 2 ሚሊዮን፣ 16 ነጥብ 3 ሚሊዮን እና 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ተይዘዋል ነው ያለው፡፡
የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 11 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ከኮምሽኑ የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድኃኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡